የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ አዲስ በተሻሻለው የፌደራል ገቢ ግብር አዋጅ ዙሪያ በከተማው ለሚገኙ የደረጃ ‘ለ’ግብር ከፋዮች ስልጠና ሰጠ ***********

( አሶሳ ፦ጥቅምት 25/2018 ዓ.ም)
የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ ከክልል ገቢዎች ባለስልጣን ጋር በመተባበር አዲስ በተሻሻለው የፌደራል ገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 1395/2017 እና ዊዝሆልዲንግ ገቢ አሰባሰብ ዙሪያ በከተማው ለሚገኙ የደረጃ ‘ለ’ ግብር ከፋዮች ስልጠና ሰጥቷል ።

በስልጠና መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአሶሳ ከተማ ገቢዎች መምሪያ ሀላፊ አቶ አኑዋር አስር እንደተናገሩት እንደ ሀገር አዲስ የተሻሻለውን የገቢ አዋጅ ተፈፃሚ ለማድረግ እና የከተማውን ብሎም የክልላችን ገቢ ለማሳደግ ግብር ከፋዮችን ቀድሞ ማሰልጠን ለውጤታማ ገቢ አሰባሰብ ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

በተጋባዥነት ስልጠናውን የሰጡት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን የግብር ከፋዮች ትምህርት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደምስ አሰፋ አዲሱን የግብር አዋጅ የደረጃ ለ ግብር ከፋዮችን በተመለከተ በሚኖረው አተገባበር እና አፈጻጸም ዙሪያ ሰፋ ያለ ስልጠና ሰጥተዋል ።

በዚህም የነባሩ የግብር ከፋዮች አዋጅ 979/2008 ማሻሻያ አዋጅ 1395/2017 ላይ በቀድሞው ሶስት (3) የነበሩት የግብር ከፋይ ደረጃዎች ወደ ሁለት ደረጃ ለውጥ የተደረገ መሆኑን ማለትም ደረጃ “ሀ” እና “ለ” ሆኖ መሻሻሉንም በስልጠናው ላይ ተጠቅሷል ።

በነባሩ የግብር ከፋዮች አዋጅ መሠረት ከዚህ ቀደም ግብር ከፋዮች በአመቱ መጨረሻ አጠቃለው አንድ ጊዜ ግብር ሲከፍሉ የነበረው እንደተተጠበቀ ሆኖ በአዲሱ የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጅ ቀጥር 1395/2017 አንቀጽ 89 ንኡስ አንቀጽ 2 እና 4 መሰረት የግብር ከፋዮች ባለፈው የግብር ዓመት የከፈሉትን ግብር 25 በመቶ በየሩብ ዓመቱ ተሰልቶ እንዲከፍሉ የሚደነግግ መሆኑን ለሰልጣኞች ተገልጿል ።

ይህም ግብር ከፋዮች በሩብ አመት የሚከፍሉት ግብር በተከታዩ አመት ሊከፍሉት ከሚገባው አመታዊ ግብር ላይ ተቀናሽ የሚደረግ በመሆኑ ለግብር ከፋዮች የጊዜ እፎይታን በመስጠት በአንድ ጊዜ ሲከፈል የነበረውን የግብር ጫና የሚቀንስም ነው ተብሏል።

የውይይት መድረኩን የመሩት የገቢዎች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤሊያስ አብዲን እንደተናገሩት የገቢ ተቋማት እና ግብር ከፋዮች አዲሱን የገቢ ግብር አዋጅ ጠንቅቀው በመረዳት ለተግባራዊነቱ እንዲሰሩ ያስገነዘቡ ሲሆን በዚህም መንግስት ማግኘት ያለበትን ገቢ በመሰብሰብ ለከተማ አስተዳደሩ የ2018 የገቢ ዕቅድ መሳካት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

በመጨረሻም ከግብር ከፋዮች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽኔ ማብራያ ተሰጥቶባቸዋል።
(መረጃው የአሶሳ ከተማ አስ/ር ገቢዎች መምሪያ ነው)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *